ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ኑሮየን በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሲያትል ዋሽንግተን በማድረግ ሳልደላደል በመኖር ላይ እገኛለሁ :: ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት አይደለም ሁለት ሳምንት የቆየሁ አይመሰለኝም :: አሜሪካ ሁለመናዋ ልዩ ነው :: እያንዳንዷ ሰዓት ገንዘብ በመሆኗና ከሚተነፈሰው አየር በስተቀር ወጪ ስለሚጠይቅ ሁሉም ኑሮውን ለማሸነፍ ይሮጣል :: የፀሐይ ነገርማ አይነሣ ፤ በአገራችን በኢትዮጵያ አስራ ሦስቱንም ወራት ፀሐይ ስንሞቅ ላደግን ለኛ ሲያትል ስንኖር የመጀመሪያው ጥያቄ ክረምት አይወጣም እንዴ ? ነው ምክንያቱም ፀሐይ በሲያትል እጅግ ውድ ናት :: እንዲያውም “የሲያትል ፀሐይና የዘመኑ ፍቅር አንድ ናቸው “ ይባላል ወዲያው ታይተው ስለሚጠፉ ::
መገናኛ ብዙኅን በሲያትል ከአርባ ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ ይናገራሉ :፡ወጣገባ በሆነችው ሲያትል የሚኖሩ ቀድመው የመጡ ኢትዮጵያውያን ወልደው ከብደው ሀብት ንብረት አፍርተው ተደላድለው ይኖራሉ :: እንደ አገር ቤት ባይሆንም በዓመት በዓል ምሳ ራት መጠራራት አለ :፡ በርካታ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች አሉ :: እንጀራው በሰልፍራይዝ ካልሆነ ከምጣዱ ስለማይወጣ መልኩ ብቻ ነው እንጀራ የሚመስለው ይሁንና ሁሉም በፍቅር ይበላዋል የዘወትር ተጠቃሚ ከሆኑ ግን ወንድም ይሁን ሴት የስድስት ወር ቅሪት የያዙ ያስመስላል::ሲያትል ውስጥ ስድስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ :: ነገር ግን ሁሉም የተለያየ አስተዳደር የሚከተሉ ናቸው : : አብያተ ክርስቲያናቱን እንደሚከተለው አቀርባለሁ ፦
በኢትዮጵያ ሲኖዶስ እንመራለን የሚሉ
፩.ደብረ መድኅኒት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን
/አረጋውያንን ጠይቄ እንደተረዳሁት በሲያትል የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ነው /
፪.ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
፫.ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
ስደተኛ በመባል በሚታወቀው ሲኖዶስ እንመራለን የሚሉ
፩.መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
/ከአንዳንድ ምዕመናን እንደተረዳሁት ረዥም ጊዜ ሲያትል ውስጥ የኖሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚሳተፉበት ነው/
ገለልተኞች ነን በሁለቱም አንተዳደርም የሚሉ
፩.ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
፪.መድኅኔዓለም ቤተ ክርስቲያን
/ሁለቱም ባለመግባባት ከደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የወጡ መሆኑን ተረድቻለሁ /
በስድስቱም አብያተ ክርስቲያናት የሚሰማው ቅዳሴ ከአንዲት ቤተ ክርስቲያን የተገኘ ዜማ ሲሆን በእየ አጥቢያው የሚያገለግሉት መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና የሚሳተፉት ምዕመናን የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጅዎች ሁነው እያለ አብያተ ክርስቲያናቱ አንድነት በሌለባት ልዩነት በመከፋፈላቸው ቤተክርስቲያኗን እየጎዳት ይገኛል:: ሲያትል ውስጥ ስላሉት አብያተ ክርስቲያናት እያንዳንዱን አጥቢያ ምን እንደሚመስል በቀጣይ የምመለስበት ሲሆን ዛሬ ወደተነሳሁበት እገባለሁ ::
ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የሆነኝ ልቤን የነካው የአንዲት ምዕመን ንግግር ነው :: ዕለቱ ዕለተ ሰንበት እሑድ ሲሆን ከቅዳሴ መልስ ወደቤቴ ሳሽከረክር እግረመንገዴን ነዳጅ ለመቅዳት ወደ አንድ ነዳጅ ማደያ ጎራ አልኩኝ በሲያትል ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ አንዲት የማውቃቸው ኢትዮጵያዊት እናት ከሁለት ሴቶችና ከአንድ ወንድ ወጣቶች ልጆቻቸው ጋር ነዳጅ ሲቀዱ አገኘኋቸው :: የእኛነታችን መገለጫ የሆኑትን የባህል ልብሶቻችንን ማማር የምናውቀው ከአገር ስንወጣ ነው :: ሰላምታ ለመለዋወጥ ከመኪናወቻችን ስንወጣ ነጫጭ ልብስ በመልበሳችን ማደያውን እንዳደመቅነው አልተጠራጠርኩም ነጮቹ ዓይናቸው ከኛ ላይ ነበር :: ስሜታቸውን መደበቅ የማይሆንላቸው አንዳንድ ፈረንጆች ስራየ ብለው ወደኛ በመቅረብ በጣም ታምራላችሁ ብለውናል ::
አራቱ ቤተሰቦች ከቤተ ክርስቲያን እንደመጡ ስላወቅኩ ከየትኛው ቤተ ክርስቲያን እንደመጡ ጠየቅኳቸው : እናት መለሱ ዛሬ ሚካኤል አይደል ከቅዱስ ሚካኤል ነው የመጣነው አሉኝ :: እኔም በርቱ በጣም ደስ ይላል በተሰብ ደግሞ ባንድ ላይ እግዚአብሔርን ሲያመልክ የበለጠ ጥሩ ነው እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ ብየ ተሰናበትኳቸው ::
ፈቃደ እግዚአብሔር ሁኖ በሳምንቱ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህን ቤተ ሰቦች አገኘኋቸው :: ሰላምታ ተለዋውጠን እንደጨረስን የቅዱስ ሚካኤል አገልግሎት እንዴት ነው ? አልኳቸው :፡ እናትም መለሱ አሁን እንኳን ከገብርኤል ነው የምንመጣው አሉኝ : ሳምንት ሚካኤል ነው የምንሄድ ብለውኝ አልነበረም ? አዎ :: ሳምንት ሚካኤል ዛሬ ደግሞ ገብርኤል :: ዛሬ ገብርኤል አይደለም እንዴ ? በማለት መልሰው እኔን ጠየቁኝ :;
ከላይ እንደገለጽኩት ቅዱስ ሚካኤል በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ሥር በመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል በስደተኛው ሲኖዶስ ሥር በመሆኑ ሚካኤልም ገብርኤልም ነው የምትሄዱት? አልኳቸው እርሳቸውም ቆፍጠን ባለ ሁኔታ እኛ አሉ እኛ ሚካኤል ሲሆን ሚካኤል ገብርኤል ሲሆን ገብርኤል እንሔዳለን ” እናንተ ቄሶቹ ተጣላችሁ እንጅ ሚካኤል እና ገብርኤል አልተጣሉም ” አሉኝ ሳቄን ተቆጣጥሬ ማሳለፍ አልቻልኩም ሴትዮዋን ከነ ቤተሰቦቻቸው ተሰናብቼ ስጓዝ ግን ለምንድንነው አባቶቻችን የማይታረቁት ? የተከፋፈለችና ለጠላት የተመቸችቤተ ክርስቲያን ትተው ለማለፍ ለምን ይሞክራሉ ? የህዝቡ ጭንቀት ፣ የቤተ ክርስቲያን መለያየት ፣የታሪክ መበላሸት እና መዛባት ለምን አይገዳቸውም ?የሚሉ ጥያቄዎች በአይምሮየ ተመላለሰብኝ በመጨረሻም አንድ ነገር መጻፍ አለብኝ ብየ ወሰንኩ ::
ይቀጥላል
May God give you the courage and good heart to continue your work! I will be looking forward to this topic..it provided much needed information in a neutral way.
ReplyDelete