የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ካስተማሩኝ መምህራን ውስጥ በተለየ መልኩ ከማልረሳቸው መምህራን የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአዲስ ኪዳን መምህር የሆኑት ደጉዓለም ካሳ አንዱ ናቸው :: ክፍል ውስጥ ለማስተማር ቀድመው ነው የሚገኙት ማርፈድ ለተማሪም ሆነ ለአስተማሪ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አላቸው :: አንድ ቀን ወደ ክፍል መግባት ከሚገባቸው ሰዓት አስር ደቂቃ ዘግይተው መጡ ሁላችንም ገርሞናል ይሁንና ማንም ያንጎራጎረ አልነበረም : ደግሞም አስር ደቂቃ ምንም አይደል::
መምህሩ ይቅርታ ጠየቁ በማስከተልም “ባለጌ” ይዞኝ ነው የዘገየሁት ቤተ ክርቲያናችን “የራሷ ባልሆኑ ባለጌዎች” ስለተሞላች ስለቤተ ክርስቲያን ስለ ወንጌል ሲነግሯቸው አይሰሙም ብለው መደበኛ ትምህርቱን ቀጠሉ ንግግራቸው ሊገባኝ ስላልቻለ ጥያቄ አለኝ አልኩ ፈሊጥ ተጠቅመው ማስተማር የዘወትር ችሎታቸው የሆነው መ/ር ደጉ መቸ ትምህርቱ ተጀመረና ጥያቄ ትላለህ አሉኝ ቤተ ክርስቲያናችን “የራሷ ባልሆኑ ባለጌዎች” ስለተሞላች ሲሉ ስለሰማሁ የራሷ የሆኑ ባለጌ ልጅዎች አሏት ወይ ለማለት ነው አልኩ ፈገግ አሉና ለመሆኑ ባለጌ ማለት ምን ማለትነው ? ብለው ተማሪዉን ጠየቁ ከጎኔ ተቀምጠው የነበሩት አንድ አባት እንዴ መምህር ባለጌማ ባለጌ ነው ሲሉ ተማሪው ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም ነበር ::
መ/ር ደጉ ሌሎቻችሁ ሞክሩ አሉ ጥሩ ሥነ ምግባር የሌለው መጥፎ ጋጠወጥ ወዘተ.....በማለት ሁሉም የእውቀቱን ሞከረ መ/ር ደጉ ግን ስለ ቋንቋ አመጣጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንሽ ካብራሩ በኋላ በቀድሞ ዘመን ይሰጥ የነበረውን ማዕረግ መነሻ አደረጉ የደብረ ሊባኖስ አስተዳዳሪ እጨጌ እንደሚባሉ የንጉሡ ባለቤት እቴጌ እንደሆኑና ለወቅቱ መንግሥት ቅርብ ነኝ የሚል ደግሞ ባለጌ እንደሚባል “ባለጌ “ማለት ባለ ጊዜ እንደሆነ ባለጊዜ /ባለጌ / እንደፈለገ እንደሚናገር ትልቁን የሚያዋርድ አቅሙን የማያውቅ እንደሆነና እጨጌ ፡እቴጌ: ባለጌ ወዘተ... ይባል እንደነበር ነገሩን ::
ዛሬም ሃይማኖት የሌላቸው ለሃይማኖት መሪዎች ቅርበት ያላቸው /ባለጊዜዎች /ስለቤተ ክርስቲያን ደንታ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ወኪሎች /ባለጊዜዎች/ መብዛታቸው ለምን ይሆን ? አርባ ዓመት የቤቴ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው በወር አርባ ብር የተነፈጋቸው ዘመናቸውን ሙሉ መምህራንን በማፍራት ያሉ የአብነት መምህራን አስታዋሽ አጥተው ምንም የቤተ ክርቲያን ትምህርት የሌላቸው ቀድሰው የማያቆርቡ የቤተ ክርስቲያኗን ቢሮ እንጅ በመቅደሱ በር የማይታዩ አስቀድሰው የማያውቁ ማስተማር የማይችሉ አንድ ቀን ተስቷቸው ጹመው የማያውቁ ፍጹም መንፈሳዊ የሚባል ነገር የማይታይባቸው ዓለማውያን /ባለጊዜዎች/ባለጌዎች/ የራሳቸውን ሥጋዊ ኑሮ መገንባት አንሷቸው ቤተ ክርስቲያኗን ለማጥፋት መሰለፍ ምን ይሉታል ?
በታሪክ በባለጌ የተሰሩ በርካታ ጥፋቶች ቢኖሩም የተመዘገበ ጥቂት በጎ ነገር የለም :: ባለጌ /ባለጊዜ ለወቅቱ ባለሥልጣን ቅርብ በመሆኑ ብቻ እንደፈለገ ሊናገር ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ሊል ይችላል መልካም ስም ስለሌለው መልካም ስም ባለበት መቆም አይችልምና መልካም የሆነውን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ደንጋይ የለም ባለጌ የተመካበትን ባለሥልጣን ጭምር ያሰድባል :: እስኪ የሽማግሌ ምርቃት ብየ ልፈጽም :
ከቶሎ አኩራፊ
ከበሽታ ተላላፊ
ከወዳጅ ሸረኛ
ከጓድኛ ምቀኛ
ከልጅ አመዳም
ከጥጃ ቀንዳም
ከቄስ ውሸታም
ከዳገት ሩጫ
ከአህያ ርግጫ
ከባለጌ ጡጫ ይሰውረን አሜ
ቀሲስ ይመችዎት ጹሑፏ ተመችታኛለች ነገር ግን :እውነት እንነጋገርና የዚህ ጹሑፍ ዓላማው ምንድን ነው ?
ReplyDeleteዓላማው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ዘመናቸውን ሙሉ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው በአገልግሎ ትእየተፋጠኑ ያሉ መምህራን የሚገባቸውን ያግኙ ፣ይታወሱ ፣ተተኪ የሚያፈሩ እነርሱ ናቸውና ትኩረት ይሰጣቸው ለማለት ሲሆን በተቃራኒው የቤተ ክርስቲያን ህይወት የሌላቸው ለሃይማኖት አባቶች ቅርበት አለን የሚሉ ባለጊዜዎች /ባለጌዎች /በቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ከሚሰሩት ክፉ ሥራ ይታቀቡ ነው :: በዚህ አጋጣሚ ባለጌዎች እናንተም ነፍስ አላችሁና እባካችሁ ወደልባችሁ ተመለሱ ከእግዚአብሔር ጋር አትጣሉ :: ቀሲስ እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛልዎ !!!
ReplyDelete