Friday, May 27, 2011

አባቶቻቻን ይታረቁ !!! ክፍል ፪

ክፍል ፪


የኢትዮጵያ ሲኖዶስ

አገራችን ኢትዮጵያ አፍሪካ ካሏት አገሮች አንዷ ስትሆን አውሮፓውያን አገራትን እንደ ቅርጫ ሥጋ ተቀራምተው ቅኝ ሲገዙ ያልተገዛችና የነጻነት ተምሳሌት ሁና በመኖሯ ስሟ በዓለም ጎልቶ የሚነገርላት ናት :: ይህ ብቻ ሳይሆን አስቀድማ ብሉይን በኋላም አዲስ ኪዳንን ተቀብላ የኖረች አገር በመሆኗ አገረ እግዚአብሔር በመባል ትታወቃለች :: እንግዳ ተቀባይና ሰው አክባሪነቷም ሌላው መለያዋ ነው :: ሌሎች ጎረቤት አገሮች የራሳቸውን ቋንቋ ባህል ሃይማኖት ሲያጡ ባህሏን ታሪኳንና ማንነቷን ጠብቃ የኖረች የራሷ ቋንቋ ከነፊደሉ ፣ሥነ ጹሑፍ ፣ኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ያላት እንዲሁም ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች ያላት መሆኗ ለአፍሪካ ኩራት እንድትሆን አድርጓታል ::

ለኢትዮጵያ ከላይ ለተዘረዘሩትና ላልተገለጹ ማንነቷ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቶያን መሆኗ የሚያነጋግር አይደለም :: ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን በሥነ ምግባር አንጻ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዝግጁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ለአገርና ለወገን የሚታመኑ ሰላማዊና አምራች እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታደርግ ናት::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምን የምትሰብክ ፣ ስለ ሰላም የምትዘምር ፣ ልዩነትን የምትጸየፍ ና የተጣላ የምታስታርቅ ስትሆን መሪዎቿም ይህን የሚያስፈጽሙ የሰላም መልእክተኞችና የፍቅር አስተማሪዎች ሊሆኑ የግድነው :: ትክክለኛ ገጽታዋ ይህ ሁኖ ሳለ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የሚታየው ልዩነት የቤተ ክርስቲያኗን ስምና ታሪክ የሚያበላሽ ሁኖ ይገኛል :: በ፲፻፱፻፹፫ ዓ.ም የደርግ መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፬ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እንድዲሁም ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከአገር መሰደድ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ከሁለት ተከፍላ በአባቶች መወጋገዝም ምዕመናን ግራ ተጋብተውና የሚያደርጉት ጠፍቶባቸው በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥፋት በቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጅወች እየተፈጸመ ይገኛል::

ስደተኛው ሲኖዶስ
             ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፣ስደተኛ ሲኖዶስ እና ገለልተኛ በሚል ተከፋፍላ ያለችሲሆን በየአጥቢያው ያለው አለመግባባትና ፍቅር መጥፋት ሳቢያ ወደ ሁሉም አንሄድም ብለው የተቀመጡትን ቤት ይቁጠራቸው ::የቀደሙት አባቶቻችን ደክመው ያሰባሰቡት ምዕመን ጠባቂ አጥቶ ሲበታተንና ወደሌላ በረት ሲገባ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሰቅቅ ነገር አለ ?

ከቀን ቀን ልዩነት እየሰፋ ችግሮች እየተባባሱ መሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን ልጅዎች እጅግ እያሳዘነና እያስለቀሰ ይገኛል ::

አባቶች መምህራነ ፍቅር እንደመሆናቸው ልዩነታቸውን በመነጋገር ፈትተው ሥልጣንን ዝናን ክብርን ሳያስቡ ላስተማረችና ለዚህ ደረጃ ላደረሰች ቤተ ክርስቲያን ይልቁንም ከእግዚአብሔር ለተቀበሉት አደራ ቅድሚያ በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ::

አባቶች ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ካልሆኑ ፣ ለመንጋው የማይራሩ ፣ የህዝብ ሀዘን የማይሰማቸው እና የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የተበታተነችና ጉልበት የሌላት እንድትሆን ካደረጉ እግዚአብሔርም ታሪክም ይጠይቃቸዋል :: ልዩነት ተወግዶ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል አባቶቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መስማማት አለባቸው ::

አሁን ያለውን ዝርዝር ችግርና የመፍትሔ ሃሳብ ከመሰንዘሬና ለውይይት ከማቅረቤ በፊት ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ሹመት ታሪክ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሣት እሞክራለሁ ::

ቤተ ክርስቲያናችን ክርስትናን በመጀመር ቀዳሚውን ስፍራ ብትይዝም ከራሷ ልጅዎች ጳጳስ መሾም ከጀመረች ገና የአንድ ጎልማሳ እድሜ ብቻ ነው ያስቆጠረች ::

የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት/ Oriental churches / ከሚባሉት ግብጽ ፣አርመን ፣ሦርያና ሕንድ ጋር አንድ ዓይነት ዶግማና ቀኖና ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በ፴፬ ዓም በጃንደረባው አማካኝነት ክርስትናን ተቀብላ ለ፪ሺ ዓመታት ስትሰብክ የኖረች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት ::

የኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ሹመት አጀማመር

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለ፩ሺ፮፻ ዓመታት በርካታ ገንዘብና ወርቅ ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን በመገበር ጳጳሳትን ስታስመጣ ኑራለች :: ለዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጡ በጉባኤ ኒቅያ ቀኖና አንቀጽ ፵፪ በስርዋጽ የገባ “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ “ የሚል ትዕዛዝ ነበር :: ይህ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጨመረ ነው ይላሉ :: በዚህ ቀንበር ማጥበቂያ ተብሎ በሚታወቀው አንቀጽ ምክንያት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጅወች እንዳትመራ ተደርጎ ለቁጥር የሚያታክቱ ዓመታት ኑራለች ::
በንጉሥ ሐርቤ

ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ቋንቋ የሚያስተምሩ ከራሷ የተገኙ አባቶች ሊሾምላት እንደሚገባ በሊቃውንቱ በተለያዩ ዘመናት ሲጠይቁ ኑረዋል :: ይልቁንም በ፲፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነግሦ የነበረው ሐርቤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ጳጳሳት እንዲሾምላት ለማድረግ ያደረገው ጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ታሪክ ሲያስታውሰው ይኖራል ::

በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተከስቶ በነበረ የመስቀል ጦርነት የተነሣ የግብጽና የኢትዮጵያ ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያትና ኢትዮጵያ ያለ ጳጳስ በመቆየቷ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ተሰብስበው በወቅቱ የደብረ ሊባኖስ እጨጌ የነበሩትን ኢትዮጵያዊ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመንበረ ጵጵስናው እንዲቀመጡ ካደረጉ በኋላ እርሳቸውም ዲቁናና ቅስና በመስጠት አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ተደርጓል ::

ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛውን ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ ልካለች በዚህ ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥልጣኔን አልለቅም አላሉም :: ይልቁንም በአገልግሎት በቆዩበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለኃላፊነት የሚበቁ ውጤታማ ጠንካራ መሆናቸውን ባፈሩት ፍሬ ባከናወኑት ተግባር አስመስክረው መንበሩን ከግብጽ ለመጡት አባት አስረክበዋል ::



አጼ ዮሓንስ

በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስቀድሞ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የቆየውንና በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ተነፍጎት የቆየውን ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባቶች ይሾሙልን ጥያቄ ዓፄ ዮሓንስ አጠናክረው ጠየቁ ምላሹ ግን አንድ ግብጻዊ ጳጳስ የነበሩትን ሦስት አባቶች በመጨመር በ፩፰፻፸፬ ዓ.ም ግብጻውያኑን አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ኤጲስ ቆጶስ ፣አቡነ ሉቃስ የጎጃም ኤጲስ ቆጶስ እና አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ኤጲስ ቆጶስ ሁነው ተሹመዋል :: አቡነ ጴጥሮስ ሲያርፉ የሸዋ ኤጲስ ቆጶስ የነበሩት አቡነ ማቴዎስ መንበረ ጵጵስናውን ይዘው በሸዋ ኤጲስ ቆጶስ ሁነው ለ ፰ ዓመታት በኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስነት ለ ፴፯ ዓመታት አገልግለዋል ::
                                                 


ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ
                                                      በንግሥተ ነገሥታት ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያውያን መልስ አጥተውበት የኖሩትን ጳጳስ ከራሳችን ወገን ይሾምልን ጥያቄ በሊቃውንቱ አማካኝነት በወቅቱ በነበሩ መገናኛ ብዙሓን /በጋዜጣ/ ሲወጣ ኅሳቡ ወደ ቤተ መንግሥት ደረሰ በዚህ ምክንያት ጉዳዩ ከቤተ ክህነት አልፎ የቤተ መንግሥት ሆነ :: በዘመኑ አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኰንን ከንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ፣ ከመሣፍንቱ ፣ ከመኳንንቱ እና ከሊቃውንቱ ጋር በመሆን ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መከሩ ::
ልዑል አልጋወራሽም ባረፉት የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ምትክ ሌላ እንዲመደቡና ከእሳቸውም ጋር በኢትዮጵያ ወንጌል እንዲስፋፋ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዲሾምላቸው በመጠየቅ በወቅቱ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለነበሩት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ አምስተኛ ደብዳቤ ላኩ ::





ፓትርያርኩም ደብዳቤው ደርሷቸው ከተመለከቱት በኋላ የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ ::

“ጉዳዩን ብቻየን ለመወሰን ስለማልችል በጉዳዩ ላይ የሚመክር ጉባኤ ጠርቼ እወያይበታለሁ “ ይህን ምላሽ ያገኙት ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንና የኢትዮጵያውያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ውሳኔውን እየተጠባበቁ እያለ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ለ ፶፪ ዓመታት ከ፱ ወራት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ማረፋቸው ስለተሰማ ረፍታቸውን ምክንያት በማድረግ አልጋ ወራሽ የሃዘን መግለጫ ላኩ :: ከዚህ ላይ የፓትርያርኩ ረፍት ተሰምቶ የሃዘን መግለጫው ሲላክ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ምልስ እንዲያገኝ አዲስ አበባ ላይ ሰባት ጊዜ መድፍ ተተኩሷል ::

አሁንም ፓትርያርኩን የሚተካ እስኪመረጥ ድረስ የኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ቆይቶ ታህሳስ ፯ ቀን ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሓንስ ፲፱ኛው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሁነው እንደተሾሙ ለልዑል አልጋወራሽ ተፈሪ መኮነን ተገለጸላቸው :: አልጋወራሹም የተሰማቸውን ደስታ ለአዲሱ ፓትርያርክና ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሲልኩ አያይዘው ከአሁን ቀደም የጠየቁት ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ጳጳስ ይሾምልን ጥያቄ አፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ አሳስበው በአቡነ ማቴዎስ ምትክ አንድ ሊቀ ጳጳስ ተሹሞ እንዲላክ እርሱም አዲስ አበባ ሲደርስ ከኢትዮጵያውያን እየመረጠ ጳጳሳትን እንዲሾም የሚል ጥያቄ ያዘለ መልዕክት ላኩ ::
አጼ ኃይለ ሥላሴ

አዲሱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ጥያቄውን ሙሉ በሙሉ ባለመቀበል አንድ ግብጻዊ ሊቀ ጳጳስ ብቻ ለመመደብ መፍቀዳቸውንና ሊቀ ጳጳሱ ከኢትዮጵያውያን ለመሾም ቀኖናው እንደማይፈቅድላቸው በመግለጥ ጳጳስ ተብለው እንዲሾሙ ብፁዕ እጨጌን እንዲላኩላቸውና ከሊቀ ጳጳሱ ጋር በኢትዮጵያ በየክፍሉ የሚራዱ ሁለት ግብጻውያን ጳጳሳት እንደሚመድቡ ምላሽ ሰጡ ::

ዲ/ን መርሻ አለኽኝ “ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን “ በሚል በ፲፻፱፻፺፯ ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ እንደገለጹት አልጋ ወራሽ ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው የሚከተለውን ሌላ ደብዳቤ ላኩላቸው ፡

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሓንስ አንድ ሊቀጳጳስ ለመሾም ከእኛም ለአንዱ እጨጌ ጵጵስና ለመስጠት መፍቀድዎን የሚገልጽ መልዕክትዎ ደርሶን ተመልክተነዋል ይሁንና እንዳሰብነው የትምህርት ችግራችንን የሚያቃልል አይደለም የሚጨመሩትም ሁለት ግብጾች ቋንቋችንን ስለማያውቁት ፈቃድዎ ሁኖ በቋንቋችን የሚያስተምሩ ሊቃውንት የሚያስፈልገንን ያህል ከመልዕክተኞቻችን ጋር ወደ እናንተ ልከን እንዲሾሙ ቢደረግ ይህ ካልሆነም የኛን ሊቃውንት ጳጳስ አድርገው ሹመው ከግብጽ የሚመደቡት ሊቀ ጳጳስ ጋር ቢልኩልን ሁለተኛው ኃሳብ ግን እስከ አሁን ጸንቶ የኖረው የአባትና የልጅነት መተማመን እንዳይጎድል እንጅ ኃሳባችን አሁንም የመጀመሪያው መሆኑን ያውቁልን ዘንድ እንለምንዎታለን ::

ልዑሉ መልዕክቱን ከላኩ በኋላ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ግብፅም ትኩረት እንድትሰጠው በወቅቱ የትምህርት ሚ/ር ዳይሬክተር በነበሩት በአቶ ሳህሌ ጸዳሉ የሚመራ ልዑክ ወደ ግብፅ ላኩ ልዑካኑም ከፓትርያርኩ ጋር ጠንከር ያለ ውይይትና ክርክር አድርገዋል ፓትርያርኩም አስቸኳይ የሲኖዶስ ስብሰባ ጠርተው ከተነጋገሩ በኋላ አንድ ግብጻዊ ሊቀ ጳጳሳት ከአምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ጋር እንዲሾሙ ፈቀዱ ::

ይህ ውሳኔም ለግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ መኰንን በቴሌግራም እንዲተላለፍ ተደረገ :: መልዕክቱም

“ ሐዋርያዊ ቡራኬያችን ለግርማዊነትዎ ይሁን ከኢትዮጵያ መምህራን አምስት ሰዎች ተመርጠው ጳጳሳት ሁነው አምስት የኢትዮጵያ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲሾሙ ፈቅደናልና አምስት መነኮሳት እንዲልኩልን እንለምናለን “

ልዑል አልጋ ወራሽም ባስቸኳይ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል :

“በሣህሌ ጸዳሉ በኩል ላስታወቅንዎ ጉዳይ ከቡራኬዎ ጋር በላኩልን ምላሽ ደስ ብሎናል መነኮሳቱንም እንደሚያስፈልግ አድርገን እንልካለን :: እግዚአብሔር ቅዱስነትዎን ይጠብቅ ::”

ይቀጥላል



Tuesday, May 17, 2011

አባቶቻችን ይታረቁ !!! ክፍል ፩

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ኑሮየን በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሲያትል ዋሽንግተን በማድረግ ሳልደላደል በመኖር ላይ እገኛለሁ :: ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት አይደለም ሁለት ሳምንት የቆየሁ አይመሰለኝም :: አሜሪካ ሁለመናዋ ልዩ ነው :: እያንዳንዷ ሰዓት ገንዘብ በመሆኗና ከሚተነፈሰው አየር በስተቀር ወጪ ስለሚጠይቅ ሁሉም ኑሮውን ለማሸነፍ ይሮጣል :: የፀሐይ ነገርማ አይነሣ ፤ በአገራችን በኢትዮጵያ አስራ ሦስቱንም ወራት ፀሐይ ስንሞቅ ላደግን ለኛ ሲያትል ስንኖር የመጀመሪያው ጥያቄ ክረምት አይወጣም እንዴ ? ነው ምክንያቱም ፀሐይ በሲያትል እጅግ ውድ ናት :: እንዲያውም “የሲያትል ፀሐይና የዘመኑ ፍቅር አንድ ናቸው “ ይባላል ወዲያው ታይተው ስለሚጠፉ ::
መገናኛ ብዙኅን በሲያትል ከአርባ ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ ይናገራሉ :፡ወጣገባ በሆነችው ሲያትል የሚኖሩ ቀድመው የመጡ ኢትዮጵያውያን ወልደው ከብደው ሀብት ንብረት አፍርተው ተደላድለው ይኖራሉ :: እንደ አገር ቤት ባይሆንም በዓመት በዓል ምሳ ራት መጠራራት አለ :፡ በርካታ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች አሉ :: እንጀራው በሰልፍራይዝ ካልሆነ ከምጣዱ ስለማይወጣ መልኩ ብቻ ነው እንጀራ የሚመስለው ይሁንና ሁሉም በፍቅር ይበላዋል የዘወትር ተጠቃሚ ከሆኑ ግን ወንድም ይሁን ሴት የስድስት ወር ቅሪት የያዙ ያስመስላል::

ሲያትል ውስጥ ስድስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ :: ነገር ግን ሁሉም የተለያየ አስተዳደር የሚከተሉ ናቸው : : አብያተ ክርስቲያናቱን እንደሚከተለው አቀርባለሁ ፦

በኢትዮጵያ ሲኖዶስ እንመራለን የሚሉ

፩.ደብረ መድኅኒት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን
/አረጋውያንን ጠይቄ እንደተረዳሁት በሲያትል የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ነው /

፪.ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
፫.ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

ስደተኛ በመባል በሚታወቀው ሲኖዶስ እንመራለን የሚሉ

፩.መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
/ከአንዳንድ ምዕመናን እንደተረዳሁት ረዥም ጊዜ ሲያትል ውስጥ የኖሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚሳተፉበት ነው/

ገለልተኞች ነን በሁለቱም አንተዳደርም የሚሉ

፩.ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን

፪.መድኅኔዓለም ቤተ ክርስቲያን

/ሁለቱም ባለመግባባት ከደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የወጡ መሆኑን ተረድቻለሁ /

በስድስቱም አብያተ ክርስቲያናት የሚሰማው ቅዳሴ ከአንዲት ቤተ ክርስቲያን የተገኘ ዜማ ሲሆን በእየ አጥቢያው የሚያገለግሉት መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና የሚሳተፉት ምዕመናን የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጅዎች ሁነው እያለ አብያተ ክርስቲያናቱ አንድነት በሌለባት ልዩነት በመከፋፈላቸው ቤተክርስቲያኗን እየጎዳት ይገኛል:: ሲያትል ውስጥ ስላሉት አብያተ ክርስቲያናት እያንዳንዱን አጥቢያ ምን እንደሚመስል በቀጣይ የምመለስበት ሲሆን ዛሬ ወደተነሳሁበት እገባለሁ ::

ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የሆነኝ ልቤን የነካው የአንዲት ምዕመን ንግግር ነው :: ዕለቱ ዕለተ ሰንበት እሑድ ሲሆን ከቅዳሴ መልስ ወደቤቴ ሳሽከረክር እግረመንገዴን ነዳጅ ለመቅዳት ወደ አንድ ነዳጅ ማደያ ጎራ አልኩኝ በሲያትል ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ አንዲት የማውቃቸው ኢትዮጵያዊት እናት ከሁለት ሴቶችና ከአንድ ወንድ ወጣቶች ልጆቻቸው ጋር ነዳጅ ሲቀዱ አገኘኋቸው :: የእኛነታችን መገለጫ የሆኑትን የባህል ልብሶቻችንን ማማር የምናውቀው ከአገር ስንወጣ ነው :: ሰላምታ ለመለዋወጥ ከመኪናወቻችን ስንወጣ ነጫጭ ልብስ በመልበሳችን ማደያውን እንዳደመቅነው አልተጠራጠርኩም ነጮቹ ዓይናቸው ከኛ ላይ ነበር :: ስሜታቸውን መደበቅ የማይሆንላቸው አንዳንድ ፈረንጆች ስራየ ብለው ወደኛ በመቅረብ በጣም ታምራላችሁ ብለውናል ::

አራቱ ቤተሰቦች ከቤተ ክርስቲያን እንደመጡ ስላወቅኩ ከየትኛው ቤተ ክርስቲያን እንደመጡ ጠየቅኳቸው : እናት መለሱ ዛሬ ሚካኤል አይደል ከቅዱስ ሚካኤል ነው የመጣነው አሉኝ :: እኔም በርቱ በጣም ደስ ይላል በተሰብ ደግሞ ባንድ ላይ እግዚአብሔርን ሲያመልክ የበለጠ ጥሩ ነው እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ ብየ ተሰናበትኳቸው ::

ፈቃደ እግዚአብሔር ሁኖ በሳምንቱ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህን ቤተ ሰቦች አገኘኋቸው :: ሰላምታ ተለዋውጠን እንደጨረስን የቅዱስ ሚካኤል አገልግሎት እንዴት ነው ? አልኳቸው :፡ እናትም መለሱ አሁን እንኳን ከገብርኤል ነው የምንመጣው አሉኝ : ሳምንት ሚካኤል ነው የምንሄድ ብለውኝ አልነበረም ? አዎ :: ሳምንት ሚካኤል ዛሬ ደግሞ ገብርኤል :: ዛሬ ገብርኤል አይደለም እንዴ ? በማለት መልሰው እኔን ጠየቁኝ :;

ከላይ እንደገለጽኩት ቅዱስ ሚካኤል በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ሥር በመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል በስደተኛው ሲኖዶስ ሥር በመሆኑ ሚካኤልም ገብርኤልም ነው የምትሄዱት? አልኳቸው እርሳቸውም ቆፍጠን ባለ ሁኔታ እኛ አሉ እኛ ሚካኤል ሲሆን ሚካኤል ገብርኤል ሲሆን ገብርኤል እንሔዳለን ” እናንተ ቄሶቹ ተጣላችሁ እንጅ ሚካኤል እና ገብርኤል አልተጣሉም ” አሉኝ ሳቄን ተቆጣጥሬ ማሳለፍ አልቻልኩም ሴትዮዋን ከነ ቤተሰቦቻቸው ተሰናብቼ ስጓዝ ግን ለምንድንነው አባቶቻችን የማይታረቁት ? የተከፋፈለችና ለጠላት የተመቸችቤተ ክርስቲያን ትተው ለማለፍ ለምን ይሞክራሉ ? የህዝቡ ጭንቀት ፣ የቤተ ክርስቲያን መለያየት ፣የታሪክ መበላሸት እና መዛባት ለምን አይገዳቸውም ?የሚሉ ጥያቄዎች በአይምሮየ ተመላለሰብኝ በመጨረሻም አንድ ነገር መጻፍ አለብኝ ብየ ወሰንኩ ::

ይቀጥላል

"ባለጌ"

የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ካስተማሩኝ መምህራን ውስጥ በተለየ መልኩ ከማልረሳቸው መምህራን የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአዲስ ኪዳን መምህር የሆኑት ደጉዓለም ካሳ አንዱ ናቸው :: ክፍል ውስጥ ለማስተማር ቀድመው ነው የሚገኙት ማርፈድ ለተማሪም ሆነ ለአስተማሪ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አላቸው :: አንድ ቀን ወደ ክፍል መግባት ከሚገባቸው ሰዓት አስር ደቂቃ ዘግይተው መጡ ሁላችንም ገርሞናል ይሁንና ማንም ያንጎራጎረ አልነበረም : ደግሞም አስር ደቂቃ ምንም አይደል::

መምህሩ ይቅርታ ጠየቁ በማስከተልም “ባለጌ” ይዞኝ ነው የዘገየሁት ቤተ ክርቲያናችን “የራሷ ባልሆኑ ባለጌዎች” ስለተሞላች ስለቤተ ክርስቲያን ስለ ወንጌል ሲነግሯቸው አይሰሙም ብለው መደበኛ ትምህርቱን ቀጠሉ ንግግራቸው ሊገባኝ ስላልቻለ ጥያቄ አለኝ አልኩ ፈሊጥ ተጠቅመው ማስተማር የዘወትር ችሎታቸው የሆነው መ/ር ደጉ መቸ ትምህርቱ ተጀመረና ጥያቄ ትላለህ አሉኝ ቤተ ክርስቲያናችን “የራሷ ባልሆኑ ባለጌዎች” ስለተሞላች ሲሉ ስለሰማሁ የራሷ የሆኑ ባለጌ ልጅዎች አሏት ወይ ለማለት ነው አልኩ ፈገግ አሉና ለመሆኑ ባለጌ ማለት ምን ማለትነው ? ብለው ተማሪዉን ጠየቁ ከጎኔ ተቀምጠው የነበሩት አንድ አባት እንዴ መምህር ባለጌማ ባለጌ ነው ሲሉ ተማሪው ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም ነበር ::


መ/ር ደጉ ሌሎቻችሁ ሞክሩ አሉ ጥሩ ሥነ ምግባር የሌለው መጥፎ ጋጠወጥ ወዘተ.....በማለት ሁሉም የእውቀቱን ሞከረ መ/ር ደጉ ግን ስለ ቋንቋ አመጣጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንሽ ካብራሩ በኋላ በቀድሞ ዘመን ይሰጥ የነበረውን ማዕረግ መነሻ አደረጉ የደብረ ሊባኖስ አስተዳዳሪ እጨጌ እንደሚባሉ የንጉሡ ባለቤት እቴጌ እንደሆኑና ለወቅቱ መንግሥት ቅርብ ነኝ የሚል ደግሞ ባለጌ እንደሚባል “ባለጌ “ማለት ባለ ጊዜ እንደሆነ ባለጊዜ /ባለጌ / እንደፈለገ እንደሚናገር ትልቁን የሚያዋርድ አቅሙን የማያውቅ እንደሆነና እጨጌ ፡እቴጌ: ባለጌ ወዘተ... ይባል እንደነበር ነገሩን ::


ዛሬም ሃይማኖት የሌላቸው ለሃይማኖት መሪዎች ቅርበት ያላቸው /ባለጊዜዎች /ስለቤተ ክርስቲያን ደንታ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ወኪሎች /ባለጊዜዎች/ መብዛታቸው ለምን ይሆን ? አርባ ዓመት የቤቴ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው በወር አርባ ብር የተነፈጋቸው ዘመናቸውን ሙሉ መምህራንን በማፍራት ያሉ የአብነት መምህራን አስታዋሽ አጥተው ምንም የቤተ ክርቲያን ትምህርት የሌላቸው ቀድሰው የማያቆርቡ የቤተ ክርስቲያኗን ቢሮ እንጅ በመቅደሱ በር የማይታዩ አስቀድሰው የማያውቁ ማስተማር የማይችሉ አንድ ቀን ተስቷቸው ጹመው የማያውቁ ፍጹም መንፈሳዊ የሚባል ነገር የማይታይባቸው ዓለማውያን /ባለጊዜዎች/ባለጌዎች/ የራሳቸውን ሥጋዊ ኑሮ መገንባት አንሷቸው ቤተ ክርስቲያኗን ለማጥፋት መሰለፍ ምን ይሉታል ?

 በታሪክ በባለጌ የተሰሩ በርካታ ጥፋቶች ቢኖሩም የተመዘገበ ጥቂት በጎ ነገር የለም :: ባለጌ /ባለጊዜ ለወቅቱ ባለሥልጣን ቅርብ በመሆኑ ብቻ እንደፈለገ ሊናገር ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ሊል ይችላል መልካም ስም ስለሌለው መልካም ስም ባለበት መቆም አይችልምና መልካም የሆነውን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ደንጋይ የለም ባለጌ የተመካበትን ባለሥልጣን ጭምር ያሰድባል :: እስኪ የሽማግሌ ምርቃት ብየ ልፈጽም :
ከቶሎ አኩራፊ
ከበሽታ ተላላፊ
ከወዳጅ ሸረኛ
ከጓድኛ ምቀኛ
ከልጅ አመዳም
ከጥጃ ቀንዳም
ከቄስ ውሸታም
ከዳገት ሩጫ
ከአህያ ርግጫ
ከባለጌ ጡጫ ይሰውረን አሜ