Wednesday, June 8, 2011

አይቻልም !!

                                                        
ወደ እሳት ውስጥ ብንጨመር  _________________ቅዱስ ገብርኤል ይመጣልናል ዳን ፫፥፩
ለአናብስት ብንሰጥ ______________________ ______የዳንኤል አምላክ አለልን :: ዳን ፮፥፳
የሞት ደብዳቤ ቢጻፍብን _______________________የባህራን አምላክ የት ሂዶ ?/ ድርሳነ ሚካኤል/
ጲላጦስ ፊት ብንቀርብ _________________________ክርስቶስ ምሳሌ ሁኖናል :: ማቲ ፳፯፥፪
ወደ እስር እንኳ ብንገባ ________________________መልአኩ ሊፈታን እየጠበቀ ነው ሐዋርያት ሥራ ፲፮፥፳፭


ደብረ ሊባኖስ ገዳም


ያስተማሩኝን አባቶች ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ምንጊዜም ስማቸውን ባነሣ አልጠግብም ፤አልሰለችም ::  ባለ ውለታወቸ ናቸውና  :: በዚህ አጋጣሚ ለቤተ ክርስቲያን ስትደክሙ አስተዋሽ ሳታገኙ ከእግዚአብሔር ብቻ ጠብቃችሁ ራሳችሁን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፋችሁ በመስጠት ያለመታከት በአገልግሎት ኑራችሁ ዐረፍተ ዘመን የገታችሁ አባቶች ዛሬም እንዎዳችኋለን ጸሎታችሁ አይለየን እላለሁ ::  
በልጅነት ዘመኔ በልቦናየ ሜዳ ላይ ወንጌል የዘሩበት አንዱ በኩረ ትጉሃን ገብረ መስቀል ይባላሉ :: በኩረትጉሃን ለቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን ቅናት እንዲሁም ለአገልግሎት የነበራቸውን ትጋት ሳስበው ምነው አባቶቻችን እነርሱን የሚመስል ሳይተኩ አለፉ በማለት እብከነከናለሁ ::



   
መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜውን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን ጥቅስ የት ቦታ እንዳለች ሲናገሩ ለሚሰማቸው ምን አይነት ተሰጥኦ አላቸው ያሰኛል ፤ማኅሌቱ እርሳቸው ከሌሉበት አይደምቅም :: “ቅዳሴ የማያስቀድስ መርጌታ ባልታሰረ  ጆንያ ምርቱን የተሸከመ ገበሬን ይመስላል” ይሉ ነበር :: በኩረትጉኃን ገብረመስቀል ታሪክ ሲናገሩ በወቅቱ አብረው የነበሩ ያህል አበጥረው አንጠርጥረው ነው ::  
ቢያስተምሩ የማይሰለቻቸው፣ ዘመናቸውን ሙሉ ሲያነቡ የኖሩ ፣ ከእጃቸው መጽሐፍ ተለይቷቸው የማያውቅ ፣በሃይማኖታቸው የሚኮሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚመሰክሩ ነበሩ ፤እኝህ አባት በምዕመናን ዘንድ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና የሚደመጡም ነበሩ ::

ከመነኮሳት አንዱ
 
ጸሎት ለበኩረ ትጉኃን  የእየ ሰዓቱ ምግባቸው ነው ::  ስለወጣቶች ሲናገሩ “ወጣቶች እናንተ ነገ ምን እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው ::”  የአገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ናችሁ ዛሬ ይህን ንግግር አትረዱት ይሆናል የምትሆኑትን ሁናችሁ ስታስታውሱት ሳታደርጉ ያሳለፋችሁት ሁሉ እንደ እግር እሳት ያቃጥላችኋልና እባካችሁ ተጠቀሙበት ስለ ቤተ ክርስቲያናችሁ እወቁ ትኮሩበታላችሁ” ይሉ ነበር ::        
በርካታ ወጣቶች ወደርሳቸው በመሄድ ይማሩ ነበር ዘመናዊ ትምህርት በቀድሞ ዘመን ስለተማሩ እንግሊዝኛ ደብለቅ እያደረጉ ሲያስተምሯቸው ወጣቶቹ በፍቅር ያዳምጧቸዋል የተለያየ  እምነት ያላቸውም ቢሆኑ ቀርበው ለሚጠይቋቸው መልስ ይሰጣሉ :: ያለ እውቀት ዝምብሎ  በጥራዝ ነጠቅ ሃይማኖታቸውን ካናናቁባቸው በኩረ ትጉሃን ይበሳጫሉ ፤ በሃይማኖት ቀልድ የለም ይላሉ::  ዛሬ በየ ዐውደ ምኅረቱ ከሚነገር የእርሳቸው አባባል አንዷን ላስነብባችሁ ::

አንድ ቀን ረዥም ዘምን ባገለገሉባት የክፍለሃገር ከተማ በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ  ወጣቶች  ጥያቄ እየጠየቋቸው እርሳቸውም እየመለሱ አብረዋቸው  ይሄዳሉ ፤ከመካከላቸው አንድ የፕሮቴስታን እምነት ተከታይ አብሮ አለ : ያስተምሯቸው የነበረው ትምህርት ስለ ጸሎተ ፍታት ነበር፤ ወጣቶቹም በተመስጦ እየተከታተሉ ሲጓዙ መንገድ ላይ አንድ አህያ ሙቶ ይመለከታሉ ፡  ከወጣቶቹ መካከል የፕሮ ቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው : እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ በኩረትጉኃን ፡ይህ አህያ ለምን ፍታት አይደረግለትም ? በስላቁ ያዘኑት አባትም  ጴንጤ ስለሆነ በማለት አሳፍረውታል ::
ነፍሳቸውን ይማርና ከሁሉም በላይ ስለጽናት ሲሰብኩ ተስፋን ያጎናጽፉ ነበር :: በሃይማኖታችሁ ጽኑ እውነትን  እስከያዛችሁ  ድረስ  በፈተና አትደናገጡ ፤ ”ፈተና የእግዚአብሔርን ኃያልነት የምናይበት ክስተት ነው”  “ፈተናን ውደዱት ወደምትፈልጉበት ለመድረስ የመግቢያ በር ነው “  ይሉ ነበር  ::
 ሃይማኖት፦ ዓይን ነው እናይበታለን ፣ጆሮ ነው እንሰማበታለን ፣አፍንጫ ነው እናሸትበታለን ፣እግር ነው እንጓዝበታለን ፣ጭንቅላት ነው እናስብበታለን  በጠቅላላው ሃይማኖት የሰውነት አካላችን ነው::  አካሉ ሲነካ የማይሰማው ማደንዘዥያ የተወጋ ብቻ ነው ከማደንዘዥያ ሲነቃ የተነካካ አካሉ ቁስል ይጠዘጥዘዋል ::  አካሉ ሃይማኖቱ ሲደፈር ወይንም ሲነካ የማይሰማው  የኑፋቄ ማደንዘዢያ የተወጋ  ብቻ ነው :: ይሁንና ከማደንዘዥያ ሲነቃ የተጎዳ  አካሉን /ሃይማኖቱን  እንደነበረ ለማድረግ አቅም ያጥረውና ሲያለቅስ ይኖራል  ::



እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 
  

ብንናገር የምንኮራባት ፣ብንኖርባት ወደ ጽድቅ የምታደርሰን ፣የታሪክ ማኅደር ፣የጥበብ መገኛ ፣ የዜማ ባለቤትና የአገር ባለውለታ የሆነችው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውለታዋ ተዘንግቶ እንድትበታተን ሲፈረድባት የማያዝን የማይሰማው ማን ነው ?   በዘመናችን የምንሰማውና የምናየው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ፈተና ለመቅረፍና ቤተክርስቲያናችንን ከመፈራረስ ለመታደግ እንነሣ ::
ዘመኑ ሃሰት የነገሠበት ዲያቢሎስ የሰለጠነበት ሁኗል :: እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሳደዱ ሊገፉ አግልግሎታቸው ሊደናቀፍ የሌለባቸው ክፉ ስም ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል፤ ይህን ደግሞ ጌታችን        “ ስለ ስሜ በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ “ ማቴ ፳፬፥፱  በማለት እንደተናገረ በጎ እያደረግን ስለስሙ ስንነቀፍ ስንሳደድ ስንጠላ  ደስ ሊለን ይገባል :: የተጠራነው ለዚህ ስለሆነ ጥርጥር በሌለበት ሃይማኖት ልንጸናም ያስፈልጋል ::
ቅዱስ ያዕቆብ  “ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደሙሉ ደስታ ቁጠሩት  :: ”  ያዕ ፩፥፪ እንዳለ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንፈተን ዋጋ ያለው መሆኑን እንወቅ ::
ፈተና ፦በእውነት እግዚአብሔርን እያገለገልን ከመጣ የምንደሰትበት እንጅ የምናዝንበት አለመሆኑን የእውነት ተጻራሪ ለሆኑ ሁሉ ማሳየት ተገቢ ነው :: ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንነቀፍ ከኛ ጋር ያለው እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ነውና አንሸበርም :: እግዚአብሔርን ሊያሸንፍ የሚችል ማንም የለምና :: “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ::”  ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲  ሥራውንም ማስተጓጎል አይቻልም ደግሜ እላለሁ ፡ በእውነት የሃይማኖትን ጉዞ በማስፈረራራት ማስቆም አይቻልም !!!  

3 comments:

  1. "በእውነት የሃይማኖትን ጉዞ በማስፈረራራት ማስቆም አይቻልም !!!"
    ቀሲስ ፋሲል አስረስ
    ትክክል
    ቃለ ህዮት ያሰማልን!!!

    ReplyDelete
  2. በጣም አስደሳች ብሎግ ነው :: ቄሶች ምንም እንደማያውቁ ይነገር የነበረውን በስራ በማሳየት አባታች እርስዎ የጀመሩት ትምህርት እጅግ በጣም ጥሩ ነው :: ነገር ግን ሰው ስለማያውቀው ብታስተዋውቁት ::

    ReplyDelete
  3. ማኅበረ ቅዱሳኖች ስንቱን ናችሁ ? ሁሉም ይሳካላችኋል :፡ ብትሰብኩ ፣ጥናት ብታቀርቡ፣ ኤግዚቢሽን ብታዘጋጁ ፣ ብትመክሩ ዲያቆን ቄስ ብትሆኑ ዛሬ ደግሞ እያንዳንዳችሁ ዘመኑ ባፈራው ኢንተርኔት በነፍስ ወከፍ ተቆጣጥራችሁ የፈለጋችሁትን ትናገራላችሁ ደግሞኮ የሰው ልብ እያንጠለጠላችሁ ነው ::እውነት ለመናገር እንዴት እንደምጠላችሁ ;አሁን አሁን ደግሞ ምን እንዳስነካችሁኝ አላውቅም ስለናንተ ተከራካሪና ጠበቃ ሁኛለሁ :: ማን ያውቃል ከእግዚአብሔር ሁናችሁ ከሆነስ ? ዝምምምምም ::

    ReplyDelete