Wednesday, June 8, 2011

አይቻልም !!

                                                        
ወደ እሳት ውስጥ ብንጨመር  _________________ቅዱስ ገብርኤል ይመጣልናል ዳን ፫፥፩
ለአናብስት ብንሰጥ ______________________ ______የዳንኤል አምላክ አለልን :: ዳን ፮፥፳
የሞት ደብዳቤ ቢጻፍብን _______________________የባህራን አምላክ የት ሂዶ ?/ ድርሳነ ሚካኤል/
ጲላጦስ ፊት ብንቀርብ _________________________ክርስቶስ ምሳሌ ሁኖናል :: ማቲ ፳፯፥፪
ወደ እስር እንኳ ብንገባ ________________________መልአኩ ሊፈታን እየጠበቀ ነው ሐዋርያት ሥራ ፲፮፥፳፭


ደብረ ሊባኖስ ገዳም


ያስተማሩኝን አባቶች ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ምንጊዜም ስማቸውን ባነሣ አልጠግብም ፤አልሰለችም ::  ባለ ውለታወቸ ናቸውና  :: በዚህ አጋጣሚ ለቤተ ክርስቲያን ስትደክሙ አስተዋሽ ሳታገኙ ከእግዚአብሔር ብቻ ጠብቃችሁ ራሳችሁን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፋችሁ በመስጠት ያለመታከት በአገልግሎት ኑራችሁ ዐረፍተ ዘመን የገታችሁ አባቶች ዛሬም እንዎዳችኋለን ጸሎታችሁ አይለየን እላለሁ ::  
በልጅነት ዘመኔ በልቦናየ ሜዳ ላይ ወንጌል የዘሩበት አንዱ በኩረ ትጉሃን ገብረ መስቀል ይባላሉ :: በኩረትጉሃን ለቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን ቅናት እንዲሁም ለአገልግሎት የነበራቸውን ትጋት ሳስበው ምነው አባቶቻችን እነርሱን የሚመስል ሳይተኩ አለፉ በማለት እብከነከናለሁ ::



   
መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜውን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን ጥቅስ የት ቦታ እንዳለች ሲናገሩ ለሚሰማቸው ምን አይነት ተሰጥኦ አላቸው ያሰኛል ፤ማኅሌቱ እርሳቸው ከሌሉበት አይደምቅም :: “ቅዳሴ የማያስቀድስ መርጌታ ባልታሰረ  ጆንያ ምርቱን የተሸከመ ገበሬን ይመስላል” ይሉ ነበር :: በኩረትጉኃን ገብረመስቀል ታሪክ ሲናገሩ በወቅቱ አብረው የነበሩ ያህል አበጥረው አንጠርጥረው ነው ::  
ቢያስተምሩ የማይሰለቻቸው፣ ዘመናቸውን ሙሉ ሲያነቡ የኖሩ ፣ ከእጃቸው መጽሐፍ ተለይቷቸው የማያውቅ ፣በሃይማኖታቸው የሚኮሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚመሰክሩ ነበሩ ፤እኝህ አባት በምዕመናን ዘንድ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና የሚደመጡም ነበሩ ::

ከመነኮሳት አንዱ
 
ጸሎት ለበኩረ ትጉኃን  የእየ ሰዓቱ ምግባቸው ነው ::  ስለወጣቶች ሲናገሩ “ወጣቶች እናንተ ነገ ምን እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው ::”  የአገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ናችሁ ዛሬ ይህን ንግግር አትረዱት ይሆናል የምትሆኑትን ሁናችሁ ስታስታውሱት ሳታደርጉ ያሳለፋችሁት ሁሉ እንደ እግር እሳት ያቃጥላችኋልና እባካችሁ ተጠቀሙበት ስለ ቤተ ክርስቲያናችሁ እወቁ ትኮሩበታላችሁ” ይሉ ነበር ::        
በርካታ ወጣቶች ወደርሳቸው በመሄድ ይማሩ ነበር ዘመናዊ ትምህርት በቀድሞ ዘመን ስለተማሩ እንግሊዝኛ ደብለቅ እያደረጉ ሲያስተምሯቸው ወጣቶቹ በፍቅር ያዳምጧቸዋል የተለያየ  እምነት ያላቸውም ቢሆኑ ቀርበው ለሚጠይቋቸው መልስ ይሰጣሉ :: ያለ እውቀት ዝምብሎ  በጥራዝ ነጠቅ ሃይማኖታቸውን ካናናቁባቸው በኩረ ትጉሃን ይበሳጫሉ ፤ በሃይማኖት ቀልድ የለም ይላሉ::  ዛሬ በየ ዐውደ ምኅረቱ ከሚነገር የእርሳቸው አባባል አንዷን ላስነብባችሁ ::

አንድ ቀን ረዥም ዘምን ባገለገሉባት የክፍለሃገር ከተማ በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ  ወጣቶች  ጥያቄ እየጠየቋቸው እርሳቸውም እየመለሱ አብረዋቸው  ይሄዳሉ ፤ከመካከላቸው አንድ የፕሮቴስታን እምነት ተከታይ አብሮ አለ : ያስተምሯቸው የነበረው ትምህርት ስለ ጸሎተ ፍታት ነበር፤ ወጣቶቹም በተመስጦ እየተከታተሉ ሲጓዙ መንገድ ላይ አንድ አህያ ሙቶ ይመለከታሉ ፡  ከወጣቶቹ መካከል የፕሮ ቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው : እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ በኩረትጉኃን ፡ይህ አህያ ለምን ፍታት አይደረግለትም ? በስላቁ ያዘኑት አባትም  ጴንጤ ስለሆነ በማለት አሳፍረውታል ::
ነፍሳቸውን ይማርና ከሁሉም በላይ ስለጽናት ሲሰብኩ ተስፋን ያጎናጽፉ ነበር :: በሃይማኖታችሁ ጽኑ እውነትን  እስከያዛችሁ  ድረስ  በፈተና አትደናገጡ ፤ ”ፈተና የእግዚአብሔርን ኃያልነት የምናይበት ክስተት ነው”  “ፈተናን ውደዱት ወደምትፈልጉበት ለመድረስ የመግቢያ በር ነው “  ይሉ ነበር  ::
 ሃይማኖት፦ ዓይን ነው እናይበታለን ፣ጆሮ ነው እንሰማበታለን ፣አፍንጫ ነው እናሸትበታለን ፣እግር ነው እንጓዝበታለን ፣ጭንቅላት ነው እናስብበታለን  በጠቅላላው ሃይማኖት የሰውነት አካላችን ነው::  አካሉ ሲነካ የማይሰማው ማደንዘዥያ የተወጋ ብቻ ነው ከማደንዘዥያ ሲነቃ የተነካካ አካሉ ቁስል ይጠዘጥዘዋል ::  አካሉ ሃይማኖቱ ሲደፈር ወይንም ሲነካ የማይሰማው  የኑፋቄ ማደንዘዢያ የተወጋ  ብቻ ነው :: ይሁንና ከማደንዘዥያ ሲነቃ የተጎዳ  አካሉን /ሃይማኖቱን  እንደነበረ ለማድረግ አቅም ያጥረውና ሲያለቅስ ይኖራል  ::



እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 
  

ብንናገር የምንኮራባት ፣ብንኖርባት ወደ ጽድቅ የምታደርሰን ፣የታሪክ ማኅደር ፣የጥበብ መገኛ ፣ የዜማ ባለቤትና የአገር ባለውለታ የሆነችው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውለታዋ ተዘንግቶ እንድትበታተን ሲፈረድባት የማያዝን የማይሰማው ማን ነው ?   በዘመናችን የምንሰማውና የምናየው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ፈተና ለመቅረፍና ቤተክርስቲያናችንን ከመፈራረስ ለመታደግ እንነሣ ::
ዘመኑ ሃሰት የነገሠበት ዲያቢሎስ የሰለጠነበት ሁኗል :: እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሳደዱ ሊገፉ አግልግሎታቸው ሊደናቀፍ የሌለባቸው ክፉ ስም ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል፤ ይህን ደግሞ ጌታችን        “ ስለ ስሜ በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ “ ማቴ ፳፬፥፱  በማለት እንደተናገረ በጎ እያደረግን ስለስሙ ስንነቀፍ ስንሳደድ ስንጠላ  ደስ ሊለን ይገባል :: የተጠራነው ለዚህ ስለሆነ ጥርጥር በሌለበት ሃይማኖት ልንጸናም ያስፈልጋል ::
ቅዱስ ያዕቆብ  “ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደሙሉ ደስታ ቁጠሩት  :: ”  ያዕ ፩፥፪ እንዳለ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንፈተን ዋጋ ያለው መሆኑን እንወቅ ::
ፈተና ፦በእውነት እግዚአብሔርን እያገለገልን ከመጣ የምንደሰትበት እንጅ የምናዝንበት አለመሆኑን የእውነት ተጻራሪ ለሆኑ ሁሉ ማሳየት ተገቢ ነው :: ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንነቀፍ ከኛ ጋር ያለው እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ነውና አንሸበርም :: እግዚአብሔርን ሊያሸንፍ የሚችል ማንም የለምና :: “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ::”  ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲  ሥራውንም ማስተጓጎል አይቻልም ደግሜ እላለሁ ፡ በእውነት የሃይማኖትን ጉዞ በማስፈረራራት ማስቆም አይቻልም !!!  

Tuesday, June 7, 2011

ለምን ይዋሻል ?


                     
አሁን ያለሁት ስታር ባክስ /starbucks/  ተብሎ በሚታወቀው በአንዱ ቡና መጠጫ ውስጥ ነው :: ጥግ ይዠ ተቀምጫለሁ :: ከአንድ ወዳጄ ጋር ለመገናኘት ስለተቃጠርን ነው ከዚህ ቦታ የተገኘሁት :፡ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ስለሚሰጡ  የቀጠሮየ ሰዓት እስኪደርስ  ላፕ ቶፕ ኮምፑዩተሬን ከፍቸ መልዕክቶች እያየሁ ነው  :: ቤቱ በበርካታ ተስተናጋጅ ተሞልቷል :: ጥቂቶቹ አሜሪካውያን ሲሆኑ ባብዛኛው ግን ሐበሻ በመባል የምንታወቅ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ነን :፡
ሐበሻ : አረቦች ያወጡልን የተሳሳተ ስማችን ሲሆን  ውጥንቅጥ ድብልቅልቅ እንደማለት ነው:: ትርጉሙን የወሰዱት ኢትዮጵያ የኩሽ ልጅዎች ሳባና አቢስ ሰፍረውባት ነበርና በስማቸው ስላስጠሯት  በሳባ የሳባ ምድር በአቢስ አቢሲንያ ስትባል ኑራለች ከዚህ የተነሣ አቢሲንያ የሚለውን ” ሓበሽ” በማለት ተርጉመው እንደሰጡን የታሪክ ጸሐፊዎች ያስረዳሉ ::
በአገራችን ማኪያቶ የሚባለው አይነት “ላቴ”/ Latte /የሚሉትን እየጠጣሁ ወዳጄን እየጠበቅኩት ነው ሥራም ሳልፈታ መልዕክት እያየሁ እየላኩ ነው ::  አንድ  ከጎኔ የተቀመጠ ሰው ኤክስኩዝሚ /excuse me/አለኝ ሥራየን አቁሜ ወደ እርሱ ዞርኩ ዱ ዩ ስፒክ አምሓሪክ  ? /do you speak Amharic ?/ እንደምችል ምላሽ ሰጠሁ :፡ በጥሩ አማርኛና ጨዋነት በተላበሰ አነጋገር ጊዜ ይኖርሃል ማውራት እንችላለን ? አለኝ:: ቀጠሮ እንዳለኝ ነገር ግን ወዳጄ እስኪመጣ ማውራት እንደምንችል ነገርኩት :፡
ታያለህ አለኝ ወደ ተስተናጋጁ እየቃኘ ምኑን አልኩት አብዛኞቻችን እኮ ሐበሾች ነን ለምንድን ነው ? ቡና የምንወድ እኛ ብቻ ነን እንዴ ? አለኝ : ምናልባት ከቡናው መፈጠሪያ ስለመጣን ይሆናል አልኩት :: የቡና መፈጠሪያ ኢትዮጵያ ናት ያለው ማን ነው ? አለ ግንባሩን ኮስኮስ አድርጎ :: ይህማ የታወቀ ነው አልኩት የማውቀውን ለማስረዳት እየተዘጋጀሁ ::  
ለምን ይዋሻል ? ኢትዮጵያ ቡና ዋንኛ የገቢ ምንጯ እንደሆነ አውቃለሁ እንዲያውም በልጅነቴ “የገቢው ምንጫችን ቡና ቡና “ የሚለውን ዘፈን በአባቴ ሰባራ ሬዲዮ ባትሪዉን በፀሐይ እያሞቅን ስናዳምጥና አብረን ስንዘፍን ትዝ ይለኛል፤ ከዚህ ያለፈ የቡና መፈጠሪያው ኢትዮጵያ እንደሆነች አላውቅም ለማመንም እቸገራለሁ ምክንያቱም ፈረንጆች አንድ አዲስ ነገር ሲያገኙ ስም የሚያወጡት ግኝቱን ባገኘው ሰው ወይንም በተገኘበት ቦታ ስም ነው የሚሆነው እናም ዛሬ ፈረንጆቹ ኮፊ /coffee/ ከማለት ቡና ባሉት ነበር እንዲያውም ቡና ማለት ቃሉ ከምን እንዳመጣነው አላውቅም አለኝ ::
ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ከፋ በተባለው ቦታ እንደሆነ ኮፊ /coffee/ ከፋ ከሚለው መምጣቱን ስገልጥለት እጀን ጨብጦ የጠፋውን እቃ እንዳገኘ ሰው አመሰግናለሁ አመሰግናለሁ በማለት ምስጋና እንዳቀረበልኝ የእጅ ስልኬ አቃጨለ የቀጠረኝ ወዳጀ ነበር ፤  ሥራ በዝቶቦት ሊዘገይ እንደሚችል ከቀጠሮአችን ሃያ ደቂቃ ተጨማሪ እንድጠብቀው ከይቅርታ ጋር ገለጸልኝ ::
ከአዲሱ ወዳጀ ጋር ወዳቋረጥነው  ጭውውት ተመልሸ ማብራሪያየን ልቀጥል ስል ሌላ ጥያቄ ጠየቀኝ :: ኮምፑዩተር /computer/ ተጠቃሚ ነህ  ? አዎ :: ፌስ ቡክ አባል ነህ ? አዎ :: ለምን ይዋሻል ? አለኝ፤ ምኑ ? የኔ ምላሽ ነበር  እኔ የገጠመኝን ላጫውትህ :: የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነኝ :፡ ከብዙ ሰዎች ጋር አገናኝቶኛል በርካታ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ ከሁሉም በላይ የድሮ የሃይስኩል ጓደኞቼን አገናኝቶኛል ::
ቤተሰቦቼ ያሉት ኢትዮጵያ ነው ከከተማ በጣም የራቀ ገጠር ውስጥ:: ትምህርቴን ለመማር የተሰቃየሁትን ሳስበው  ብዙ ጥያቄዎች በአእምሮየ ይመላለስብኛል  :: ህይወቴ በሙሉ የስቃይ ጉዞ ነው ብል ማጋነን አይደለም :: ትምህርቴን ለመማር በቀን ደርሶ መልስ የስድስትና የሰባት ሰዓት መንገድ መጓዝ ይኖርብኝ ነበር  :: የርሃቡንና ጥሙ ጉዳይ  አይነገር :: ለኔ ትልቁ ተስፋ ትምህርቴ በመሆኑ ሁሉንም ተቋቁሜ እማር ነበር :፡ ከትምህርት ቤት ትዝታየ አንዷንና ህይወቴ የተቀየረበትን ልንገርህ :
የከተማ ልጅ ነህ የገጠር ? አለኝ :: ከተማ ነው ተወልጀ የደግኩ መለስኩለት :፡ ይሁን ግዴለም ::  ቀኑ ሐሙስ ነበር  በማለት ጀመረ ሐሙስ የቀን ቅዱስ ለኔ ግን ...... አልጨረሰውም ረቡዕ  ትምህርት ውየ  ለከብቶች የሚሆን ሳር አጪጄ  ቀጣዩ ቀን ፈተና ስለነበረኝ  በጨረቃ ሳጠና አድሬ  ሊነጋጋ ሲል እንቅልፍ ጣለኝ  ከእንቅልፌ ስነቃ  አንድ ሰዓት ሁኗል :: እንዴት ልግለጽልህ ? ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ ፈተናው የሚጀመረው ሁለት ሰዓት ላይ ነው ምምህሩ እንዳናረፍድ በጣም አስጠንቅቀውናል :: ምን ላድርግ ክንፍ አውጥቸ አልበር::  አባቴን ፈረስ እንዲፈቅድልኝ ለመንኩት እርሱ ደግሞ ነፍሱን ይማረውና ስለትምህርት ስለማያውቅ ሥራ እንደመፍታት ይቆጥረው ስለነበር ሁልጊዚ የሚመክረኝ ጠንካራ ገበሬ እንድሆን ብቻ ነው ::
ፈረሱን ለዛሬ ብቻ ፍቀድልኝ ጋልቤ ካልሄድኩ ለፈተና አልደርስም ብየ ተማጸንኩት አባቴ ግን ፍጹም ሊረዳኝ አልቻለም በመጨረሻ ሳላስፈቅድ ወስጀ ፈተናውን ተፈትኘ ቢጣላኝ እንኳን በሽማግሌ እታረቃለሁ በሚል  ፈረሱን ሰርቄ እየጋለብኩ ወደ ከተማ ሸመጠጥኩ :: እንዳዛን ዕለት በፈረስ ሩጨ አላውቅም  አንድ ሁለት ጊዜ ልወድቅ እግዚአብሔር አውጥቶኛል :: እንደምንም ለሦስት ሩብ ጉዳይ ከተማ ደረስኩ :: ፈረሱን አንድ የማውቃቸው ሰዎች ለምኘ ከነርሱ ግቢ ካሰርኩት በኋላ እየሮጥኩ ወደ ት/ቤት ስደርስ ፈተናው ተጀምሯል :: መምህሩን እንዲያስገቡኝ ጠየቅኩ ፈተናው ከተጀመረ ቆይቷል ስለዚህ መግባት አትችልም አሉኝ :: እንባ እየተናነቀኝ እባክዎን ተጨማሪ ሰዓት አይስጡኝ እንደሚያዩኝ የገጠር ልጅ ነኝ ሳጠና መሽቶብኝ አሁንም የመጣሁት በፈረስ ነው  በማለት የሆነውን ሁሉ በማስተዛዘን ነገርኳቸው በትክክል ያዳመጡኝ አይመስለኝም  ወንድሜ ዛሬ መግባት አትችልም ብለው በሩን ላዬ ላይ ዘጉብኝ :: ያለቀስኩትን ለቅሦ አልረሳውም የኪዳነ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን  በአቅራቢያው ስለነበር ወደዚያ በመሔድ እንባ ሳይሆን ደም አለቀስኩ ::



እንባየን ጠራርጌ እንደተነሣሁ  አዕምሮየ በደንብ ማሳብ ተስኖት ነበር እንደምንም ራሴን ለማረጋጋት ሞክሬ ቤቴን ለመመለስ ወሰንኩ::  እኩለ ቀን ሊሆን ምንም አልቀረው ፈረሱን ወዳሰርኩበት ቤት አመራሁ :: ስደርስ ግን ዓለም በኔ ላይ እንዳመጸችብኝ ነው የተሰማኝ ያሰርኩት ፈረስ ከቦታው የለም ::  እንደ አበደ ሰው ሆንኩኝ ደግሞም አብጃለሁ :: ግራውን ቀኙን ብቃኝ ፈረሱ የለም :: ሰዎቹን ጠየቅኳቸው አላየንም አሉኝ ::
ምን ላድርግ የቅርብም ሆነ የሩቅ ዘመድ ከተማ ውስጥ የለኝም ለማን ላወያየው ስቅስቅ ብየ አለቀስኩ ለመንግሥት ተናግሬ አንድ ነገር ቢረዱኝ በሚል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሳመራ የማውቃቸው ከአገር ቤት የመጡ ሁለት ወጣቶች አገኘሁ ሲያዩኝ ልደበቅ አስቤ ነበር ይሁንና ፊት ለፊት ስለተገጣጠምን አልቻልኩም በፍጥነት ወደኔ ተጠግተው ምነው ? ምን ሆንክ ?አሁን እኮ አባትክን አግኝተናቸው ሰላም እንኳን ሳይሉን ፈረሳቸውን እየጋለቡ ወደ ቤታቸው ሄዱ ምን ሁናችኋል ? አሉኝ :: ፊቴ በደስታ ፈካ  አባቴ ፈረሱን የምሸጥበት መስሎት ተከታትሎ መውሰዱ ነው ::
ልጅወቹ ምንግሥት  ወታደርነት አሰልጥኖ ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ሊመዘገቡ እንደመጡ አጫወቱኝ እድሉ ጥሩ እንደሆነና እኔም ልጠቀምበት እንደሚገባ መከሩኝ ፤የማስብበት አዕምሮ ስላልነበረኝ በምወደውና ተስፋየ ባልኩት ትምህርቴ ጨክኘ እኔም ከነርሱ ጋር ተመዘገብኩ ::
ወደ ወታደር ማሰልጠኛው ስንጓዝ በፈቃዴ ወደ ሞት የምሄድ ያህል ይሰማኝ ነበር ወታደራዊ ሥልጠናው ከከተማ ለመጡ ልጅዎች ትንሽ የከበዳቸው ቢሆንም በግብርና  ስንኖርን ለቆየን ድካሙ ምንም አላስቸገረንም :: ሥልጠናው እንደተጠናቀቀ በትምህርት ደረጃችን መሰረት የተለያዩ ቦታወች ተመደብን :: እኔም የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ስለነበርኩ ትምህርቴን እየተማርኩ የምሰራበት እድል አግኘሁ ::
በጪውውታችን መሃል አንድ ሰው ተከሻየን ነካ አደረገኝ የቀጠረኝ ወዳጀ ነበር :: ከአዲሱ ወዳጀ ጋር የጀመርኩት ጭውውት ስላልተቋጨ እኔም በተራየ ጥቂት ደቂቃዎች እንዲሰጠኝ በመጠየቅ ጭውውታችን ቀጠልን : ይቅርታ አለ ዐይኑ ላይ ያለው እንባ በጉንጮቹ መንታ ሁኖ እየወረደ :: ይቅርታ አሰለቸውህ : ከዚህ አገር ቁጭ ብሎ ብሦትህን የሚያዳምጥህ የለም በድጋሜ አመሰግንሃለው አለኝ ::
ምንም አታስብ ብዙ ነገር እየተማርኩ ነው የጀመርከውን ቀጥልልኝ አልኩት :፡ ጊዜህን ላለመሻማት ወታደር ቤት ሁኘ ማትሪክ ተፈተንኩ ውጤቴ ጥሩ ነበር ዩንቨርስቲ መግባት እችል ነበር ይሁንና ዲቪ ደርሦኝ ወደዚህ መጣሁ :: የኔ ነገር የተነሳሁበትን ጉዳይ ትቸ ባለፈ ነገር አደከምኩህ :: ገጠር በማደጌ ዓይናፋር ነኝ ወታደር ቤት ጥቂት ጊዜ ብኖርም ምንም ያህል አልለወጠኝም :፡በተለይም ከሴቶች ጋር አፌን ሞልቸ ማውራት እፈራለሁ የወንድ ጓደኛም ቢሆን የለኝም ሚስት ለማግባት ካሰብኩ ሰነበትኩ ግን እንዴት ተብሎ ?  የሚንቁኝ ይመስለኛል ::

         

 አንድ የተሻለ አማራጭ አገኘሁ ዘመኑ ባመጣው ፌስ ቡክ የተዋወቅኳት አንዲት አዲስ አበባ የምትኖር ኢትዮጵያዊት ከብዙ የኃሳብ ልውውጥ በኋላ ስልኳን ሰጠቸኝ  አንድ እሑድ ስፈራ ስቸር ደወልኩላት ስልኩን ያነሳው ወንድ ሲሆን ስሟን ጠቅሸ እንዲያገናኘኝ ለመንኩት በጨዋ አነጋገር አንዴ ይጠብቁ ካለኝ በኋላ ድምጿን ሰማሁት :: ማንነቴን ገልጨላት ላናግራት ስሞክር በሹክሹክታ ሌላ ጊዜ እንድደውል አሁን ከቤተሰቦቿ ጋር እንደሆነች ነገረችኝ ::
ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ይቅርታ ያዘለ መልዕክት በፌስ ቡክ ላከችልኝ : ስልኩን ያነሣው ታላቅ ወንድሟ እንደሆነና   ማንነው ? ብሎ እንዳፋጠጣትም አከለችበት :: የሚመቻትን ሰዓት ጠቆመችኝ ፤እኔም ምንም ማለት እንዳልሆነ ባለችው ሰዓት እንደምደውልላት ገልጨ መልስ ሰጠሁ :: በተባለው ሰዓት ስደውል ህፃን ልጅ ነበር ያነሳው :: አባባ ! አለኝ ማሙሽ ደህና ነህ  ? እኔ ማሙሽ አይደለሁም: አቢቲ ነኝ ማነው የሚል የሴት ድምጽ ሰማሁ ስልኩን ከልጁ ተቀብላ ሃሎ አለችኝ ማንነቴን አሳውቄ ደስ የሚል ህጻን ነው አልኳት የታላቅ ወንድሟ ልጅ እንደሆነና አንተም ለከርሞ ይኖርሃል ብላ ቀልድ ቢጤ ጣል አደረገች አመሰገንኳት ::
እንግዲህ ትውውቃችን በዚህ ጸንቶ ቤተሰቦቿ ጋር ስለምትኖር በፈለግኩበት ሰዓት በስልክ ላገኛት ባልችልም በተባረከው ፌስ ቡክ እየተገናኘን የለጠፈቻቸውን ፎቶ ግራፎቿን በየጊዜው እያየሁ እጅግ በጣም ወደድኳት ከፎቶወቿ ሦስት የሚሆኑትን መርጨ በማሳጠብ ክፍሌ ውስጥ ሰቅያለሁ :: ለፍቅሬ መግለጫ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ገዝቸ ላኩላት : ምስጋናዋ አንጀት ያርሳል ::
በመጨረሻ ቀለበት ማሰር እንዳለብንና  በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ እንደሆነ ፊት ለፊት ላያት እንደጓጓሁ ገለጽኩላት :: ትንሽ መቆየት እንዳለብኝ ቤተሰቦቿ  አስቸጋሪ እንደሆኑ እስክታሳምናቸው እንድታገሳት አጥብቃ ለመነችኝ :: ኃሳቧን ተቀብየ ትንሽ ከቆየሁ በኋላ መታገስ ስላልቻልኩ ያለችኝ ሳንቲም ቋጥሬ በአብዛኛው ለእጮኛየ የሚሆኑ ስጦታዎችን ይዠ ሳልነግራት ወደ ሀገሬ በረርኩ ::